የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክርቤት

Addis Ababa Media Council
/
በሞያሌው ግጭት፤ በክልል አቀፍ መስፋፋት እና በብሔር ፌዴራሊዝም አደጋዎች ዙሪያ የተሰጠ አጣዳፊ መግለጫ!!!
/
ቀን፤ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም.
/
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክርቤት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ በሆነችው ሞያሌ ከተማ የተቀሰቀሰውን አውዳሚና የብሔር መልክ የያዘውን ግጭት፤ እያደረሰ ያለውን የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት እና የጅምላ መፈናቀል አጥብቆ ያወግዛል። በከተማዋ የሶማሌ ክልል ባንዲራ መሰቀልን መነሻ አድርጎ የተነሳው ውዝግብ ወደ ከባድ የጦር መሣሪያ ግጭትና የተኩስ ልውውጥ ተሸጋግሮ የበርካታ ንፁኃንን ሕይወት መቅጠፉ፣ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች በእሳት መጋየታቸው እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጎረቤት ኬንያ መሰደዳቸው እጅግ አሳሳቢ አገር አቀፍ ቀውስ መሆኑን ምክር ቤቱ ይገነዘባል።

ይህ በሞያሌ የተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ብቻውን የታየ የተናጠል አጋጣሚ ሳይሆን፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እየፈጸመው ያለው የግዛት ማስፋፋት እና ወረራ ፖሊሲ ቀጣይ አካል መሆኑን እንረዳለን። ይህ ሂደት ወደፊት ለምትፈጠረው “ታላቋ ኦሮሚያ” የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት መሆኑን ፍንጭ የሚሰጥ ሲሆን፤ የብሔር ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጎሳና በነገድ እየተዋጉ በዘላቂ ጦርነትና አለመረጋጋት ውስጥ እንደሚዘልቁ ያሳየ አንዱ ግልጽ ማሳያ ነው።

ይህንን የጦረኛና ተንኳሽ ፖሊሲ አዝማሚያ ሲገመገም፤ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ፖለቲካዊ እርምጃዎችና ንግግሮች ከቀውሱ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፤ ከአንድ ዓመት በፊት የብልፅግና ፓርቲ ቁንጮ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተገኝተው “ድሬዳዋ የኦሮሚያ መሬት ናት” በሚል ያሰሙት ፀብ ቀስቃሽ ንግግር በሶማሊዎች ዘንድ ትልቅ ቁጣና አለመተማመን መቀስቀሱ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ መልኩ፤ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ከሶማሌ ክልል ጋር በነበረ የድንበር ውዝግብ መቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ፤ ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “የአዲስ አበባን ሕዝብ ስርጭት ዲሞግራፊ በኦሮሞ ተፈናቃዮች በማስፈር እንለውጠዋለን” ማለታቸው እና ተግባራዊ ለማድረግ መሞከራቸው በወቅቱ የተስተዋለ ስልታዊ ዕቅድ ማሳያ ነው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የኦህዴድ/ኦነግ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አጎራባች ክልሎች ላይ የድንበር ግጭቶችን መፍጠራቸው፤ ንፁኃንን ማፈናቀላቸው እና የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸማቸው ከዚህ የከፋ ፖለቲካዊ ስልት የመነጨ ነው። የዚህ ሁሉ አካሄድ የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን አፍርሶ በፍርስራሿ ላይ “ኦሮሚያ ሪፐብሊክን” ለመመሥረት የሚደረግ የማይሳካ የቀቢፀ ተስፋ ከንቱ ሕልም እቅድ ተግባር መሆኑን የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክርቤት በጥብቅ ያሳስባል።

በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ ሚዲያ ካውንስል በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአርሲ ዞንና በምሥራቅ ወለጋ በንጹሐን ዜጎች፣ በእምነት ተቋማትና በምዕመናን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ተደጋጋሚና አሰቃቂ ጥቃቶችን፣የሕይወት ማጣትንና የንብረት ውድመትን በጽኑ ያወግዛል። ባለፈው 2018 ዓ.ም ብቻ ከአራት ጊዜ በላይ በአርሲ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጭፍጨፋ የተፈጸመ ሲሆን፤ ድርጊቱ በዋናነት ላለፉት ሰባት ዓመታት በተከታታይ ሲፈጸም እንደነበረና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ውድመትም በሰፊው ሲደረግ መኖሩ ይታወቃል። በተለይም በአርሲ ዞን በሺርካና በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በቢርቦ፣ ጮሌ፣ ሄላ ዘንባባ እና ሶሌ ጉና ቀበሌዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች የበርካታ ህፃናት፣ሴቶችና ንጹሐን ምዕመናን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ማለፉ፤ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውና አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው የሕዝባችንን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ አሳዛኝ ክስተት ነው።

ከዚህም በላይ፤ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ «ዓሊ» ቀበሌ በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት በአንድ ቀን ብቻ ከ200 በላይ ንጹሐን ዜጎች በግፍ መገደላቸውና ከ100 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁ ሰብአዊ ቀውሱን እጅግ አከብዶታል። ቀደም ሲል ከአንዶ ዴዲቾ፤ ከመለከታ፤ ከመንደር ሶስት እና ከዋጃ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዓሊ ቀበሌ ተጠልለው የነበሩ ከ30 ሺህ በላይ ወገኖች በተከፈተባቸው አዲስ ጥቃት ሳቢያ ንብረታቸውን ጥለው አንገር ወንዝን በመሻገር ለሁለተኛ ዙር ወደ ጫካ ለመሸሽና ለአሰቃቂ እንግልት ለመዳረግ ተገደዋል።

ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!!

ማንኛውንም ዓይነት በማንነት፣ በእምነት ወይም በፖለቲካዊ ምክንያት በዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና እልቂት ካውንስሉ በፅኑ ያወግዛል። የዜጎችን ሕይወት የመጠበቅ፤ የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የሰብዓዊ መብቶችን የማስጠበቅ የመንግሥት ተብዬው እና የጸጥታ አካላት ዋነኛ መንግሥታዊ ግዴታ ነው። ጥቃት አድራሾቹ ኦነግ ሸኔ እና የዋሃቢ አክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ከኦሮሚያ ክልል የጸጥታ መዋቅር ጋር እንዲሁም በውጪ ከአልሸባብና አይኤስ አይኤስ ጋር በትብብር ጥቃቱን እንደሚፈጽሙና በጥቃቶቹ ወቅት የአካባቢው የፌደራል እና የኦሮሚያ የጸጥታ አካላት “ትዕዛዝ አልተቀበልንም” በሚል ምክንያት አፋጣኝ ደራሽነት ሳያሳዩ መቅረታቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ2018 ዓ.ም ግንቦት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በአርሲ ጭፍጨፋ ዙሪያ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት” የተገደሉት ንጹሐን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሶስት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ፤ አብዛኞቹ ደግሞ ጥቃቱን ሊከላከሉ የመጡ የኦሮሚያ ክልል ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች ናቸው ” በማለት ምክርቤቱን ለጨፍጫፊዎቹና ለተባባሪዎቹ ያስጨበጨቡላቸውን የኦሮሚያ ሚሊሻዎች በመጥቀስ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት ማደብዘዛቸው እና መሳለቃቸው፣የተበዳዮችን ቁስል የሚንቅ እንዲሁም ችግሩን ከማሳነስ ባለፈ ኃላፊነትን የመሸሽ ተግባር በመሆኑ ድርጊቱን በጽኑ እንድንቃወመው ያደርገናል።

ስለሆነም ሚዲያ ካውንስሉ ይህንን ዘረኛ፣ ጦረኛና ተስፋፊ ድርጊት አጥብቆ እያወገዘ፤ በሞያሌ ከተማና በአዋሳኝ አካባቢዎች የተጀመረው የሰራዊትና የሚሊሻዎች ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም እና የጸጥታ ኃይሎች ከከተሞች እንዲወጡ አጣዳፊ ጥሪ ያቀርባል። ከዚሁ ጎን ለጎን ለተፈናቀሉና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብና የኬንያ ድንበር አቋርጠው ለተሰደዱ ዜጎች ደህንነት ትኩረት እንዲሰጥ እያሳሰበ፤ በአርሲ፤ በወለጋና በሌሎችም ስጋት ባሉባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ንጹሐን ዜጎች አስፈላጊው የጸጥታ ጥበቃና ሰብዓዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በተጨማሪም በጥቃቶቹ ላይ የተሳተፉ፤ ያደራጁና ድጋፍ የሰጡ አካላት በሙሉ ያለ ምንም ልዩነት ገለልተኛ ማጣራት በዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ተደርጎ የብልፅግና አገዛዝ ባለስልጣኖች ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።

የክልል ድንበሮችን በኃይልና በወረራ ለመለወጥ የሚደረጉ ቅስቀሳዎችና ፖለቲካዊ ሴራዎች በአገር አንድነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጥሉ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቾና፣የማሕበረሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ታሪካዊና ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በጥብቅ ያሳስባል። በዜጎች መካከል ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ አሠራሮችና የማንነት ፖለቲካ ግጭቶች ተገርተው፤ የሁሉንም ዜጎች እኩልነት፤ ደኅንነትና ሕይወት የሚያስከብር ዘላቂ መዋቅራዊና አገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይገባል። ሁሉም የመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞችም የሕዝብ ወገንተኝነታቸውን በማሳየት፤ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በመዘገብ የንጹሐንን ድምፅ እንዲያሰሙና ለፍትሕ እንዲቆሙ ካውንስሉ ጥሪውን ያቀርባል።

ታሪክ ይህንን ቀን ይጽፋል። እኛም የዝምታን አጥር ሰብረን የሰዎችን ሰብአዊ መብትና ሕይወት ለማስከበር ድምፃችንን እናሰማለን።

ስንተባበር እንጠነክራለን፤ እናሸንፋለን!!

የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት

ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም.