የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክርቤት
Addis Ababa Media Council

አዳነች አበቤ ለሁለተኛ ገዜ በከንቲባነት በአገዛዙ መሾማቸውን በጥብቅ እናወግዛለን!!!

መስከረም 22፣ 2019 ዓ.ም

የብልፅግና አገዛዝ በግንቦት 2018 ዓ.ም ያለ ምር ተቀናቃኝ የይስሙላ ምርጫ አካሂዶ አሸነፍኩ ካለ በኋላ፤ በወረሃ መስከረም 2019 ዓ.ም «የመንግስት ምስረታ» የሚለውን ድራማ በመተወን ላይ ይገኛል።
በዚህ ሂደት ፍጹም አምባገነኑ ኦህዴድ/ብልፅግና በመላ ሀገሪቱ ያሉ ቁልፍ ተቋማትን እና የስልጣን እርከኖችን ይበልጥ እየተቆጣጠረ መሆኑን እያየን ነው።

ለዚህ እወነታ አንድ ማሳያ የሚሆነው፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በስልጣን ላይ የነበሩት “የታላቋ ኦሮሚያ” አቀንቃኟ ወ/ሮ አዳነች አበቤ እንደገና ለአዲስ አበባ ከንቲባነት መሾማቸው ብቻ ሳይሆን፣ በዙሪያቸው የሰበሰቧቸው ፀረ–አዲስ አበቤ የኦህዴድ ካድሬዎች ይበልጥ በቁጥር እንዲበዙ መደረጋቸው ነው ።

ይህ የአክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኞች ጋጋታ የከተማዋን ነዋሪዎች ይበልጥ የሚያፈናቀል፣ የከተማዋን ታሪካዊ ቅርሶች የሚያውደም እና ዝቅተኛው የከተማዋ ነዋሪ በከፋ የኑሮ ውድነት ጫና ይበልጥ እንዲሰቃይ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በአዳነች አበቤ የሚመራውን የከተማዋን የአፓርታይድ ካቢኔ እና በስሩ ያሉትን መዋቅሮች ሁሉ አጥብቆ ያወግዛል፣ አጥብቆ ይታገላል።

አዳነች አበቤን መልሶ በኃላፊነት ማስቀጠል ማለት አዲስ አበቤው በአድሏዊ የአፓርታይድ አገዛዝ ስር እንዲማቅቅ ማድረግ እና በሀገሪቱ ግዜውን ጠብቆ ለሚፈነዳ ሌላ ተጨማሪ መከራ መጋበዝ ማለት ነው። የከተማዋ አስተዳደር በኦህዴድ የበላይነት ተይዞ ከአንድ ማህበረሰብ ብቻ በተመዘዘ የጥቅም ኔትወርክ የህዝብ ሀብት እንዲዘረፍ ማድረግ ለግዜው የሚቻል ቢሆንም፣ ዘላቂነት ግን አይኖረውም።

የአዲስ አበባ ተወላጆች ለመናኛ የወረዳ ኃላፊነት እንኳን የማይታመኑበት አፓርታዳዊ አካሄድ፣ አገዛዙ ራሱ በሚምልበት ሕገ-መንግስት ተብዬ የተደነገገውን «ራስን በራስ የማስተዳደር መብት» በግላጭ የሚጥስ እና የአዲስ አበባ ህዝብ ሀገራዊ ማንነቱን የሚያከብሩ፣ የታሪኩን ጥልቀት የሚያውቁ፣ የጂኦግራፊውን አውድ እና የህዝቡን ስነ-ልቦና የሚረዱ አስተዳዳሪዎች እንዳያገኝ የሚያደርግ ነው። በዚህ የተዛባ ሁኔታ የሚጎዱት የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። አዲስ አበባ ከተማ ብቻ አይደለችም፣ የሀገራችን ሞተር ናት። ሁሌም ቢሆን የአዲስ አበባ ህመም የመላ ኢትዮጵያዊያን ህመም ነው።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት በያዝነው አዲስ ዓመት ከመላ ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆኖ፣ ሀገራችን ውስጥ የተሟላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እና አስተማማኝ ሀገራዊ እንድነት እንዲሰፍን የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል።

ስንተባበር እንጠነክራለን፣ እናሸንፋለን!!

የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክርቤት
መስከረም 22፣ 2019 ዓ.ም