የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት
Addis Ababa Media Council
—
የኦህዴዱን ዶ/ር ብርሃኑ እና የሸኔውን ቦሬ ለሚ የተናበበ ፀረ–አዲስ አበባ ዘመቻ እናወግዛለን !!!
—
ነሃሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም
—
አዲስ አበባን አስመልክቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል እና በፌዴራል አገዛዙ ውስጥ ካሉ አካላት፣ እንዲሁም ከኦነግ/ሸኔ በኩል እየተንጸባረቁ ያሉ መግለጫዎች፣ ጉዳዩ ከተለመደው የፖለቲካ ሐሳብ ልውውጥ ባሻገር፣ ስልታዊ በሆነ መንገድ እየተናበቡ አዲስ አበባን በኦሮሚያ ክልል ሥር ለመጠቅለል የሸረቡት ሴራ መሆኑን አዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት እየታዘበ ይገኛል። የሁለቱ አካላት ሐሳብ እና አካሄድ በይዘትም ሆነ በግብ አንድ መሆኑን ተገንዝበናል፤ ይህንንም አደገኛ አካሄድ በአጽንኦት እናወግዛለን።
በአንድ በኩል፣ ከኦህዴድ/ብልፅግና እንደ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ባሉ ባለስልጣናት በኩል “አዲስ አበባ በታሪክ የኦሮሞ መሬት እና ንብርት መሆኗን” በመጥቀስ፣ ከተማዋን የክልሉ አካል የማድረግ ፍላጎት በ አገዛዙ “የምክክር መድረኮች” እንዲራመድ በአደባባይ ሲሞገት እያየን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንደ ቦሬ ለሚ ያሉ የኦነግ/ሸኔ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዎች ከተማዋ “የኦሮሚያ እምብርት” መሆኗን እየገለፁ፣ የኦሮሞ ህዝብ ከከተማዋ መቆርቆር ጀምሮ እስከ አሁን ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን እና ጉዳዩ “አይነኬና አበይት አጀንዳ” መሆኑን አፅእኖት በመስጠት ከታጣቂው በኩል የአደባባይ ጫና ይፈጥራሉ። ሁለቱም አካላት ከተማዋን በባለቤትነት ለመጠቅለል የሚያደርጉት ትንተና አንድ ዓይነት መነሻ እና መድረሻ እንዳለውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።
በተጨማሪም፣ የኦነግ/ሸኔው ቦሬ ለሚ ኦህዴድ/ብልፅግና የከተማዋን ጉዳይ ለድርድር ማቅረቡ ራሱ ስሕተት መሆኑን በመግለጽ፣ ድርጊቱ የኦሮሞ ህዝብን እንደሚያስቆጣ ያስጠነቅቃሉ። በመንግሥት ሥልጣን ላይ እና መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አካላት ከእኝህው የሸኔ ቃል አቀባይ ተቀብለው ደግሞ፣ አሁን የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው በሚባለው ሕወሓት ስሪቱ ሕገመንግስት አንቀጽ 49 ያለው “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም መብት” ጠባብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ይሰነዝራሉ። ይህ የሚያሳየው ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት እስከ ታጣቂው ድረስ ያለው ኃይል አዲስ አበባን በኦሮሚያ ለመጠቅለል የተናበበ ፖለቲካዊ እና ስልታዊ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዲፕሎማሲያዊ መዋቁርም ጭምር ለህገ-ወጥ አጀንዳዎች መሸፈኛ እየሆነ መምጣቱ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል። በሳውዲ አረቢያ አምባሳደር በመሆን የሰነበቱት እና አሁን በአገር ውስጥ በአገዛዙ ምክክር ተብዬ ሂደቶች ላይ ተሳታፊ ሆነው የሚገኙት አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባን በሚመለከት በተሳታፊዎች ላይ አምባገነናዊ ዱላ ቀረሽ ስድቦችን ሲያወርዱ እና ከተመደቡበት ቡድን ውጪ በኃይል እየገቡ ሲያስቸግሩ መሰንበታቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል።
ውድ የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆይ!!
ታሪካዊውነቱ እና እውነታው ሊካድ የማይችለው ቁምነገር፤ አዲስ አበባ የሀገሪቱ የነፃነት፣ የአብሮነት እና የኩራት ማዕከል ሆና ያደገች ናት። ከተማዋ ከ1600 ዓመታት በፊት ከተመሰረተችበት ግዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ አንድ ብሔር ለብቻው የገነባት ሳይሆን፤ መላ ኢትዮጵያዊያን በላባቸው፣ በወዛቸው፣ በእውቀታቸው እና በጉልበታቸው በጋራ ሰርተው ያቀኑአት፣ የሁሉንም የዜጎች እምቅ አቅም የያዘች የጋራ የቤት ውርስ ናት።ከዚያም ባሻገር የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት።
ስለሆነም፣ የዚህችን የብዙዎች ላብ እና እውነት ያረፈባትን ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊት ማዕከል ለአንድ ብሔር ብቻ ሰጥቶ መደምደም ወይም ብቸኛ የክልል ይዞታ ማድረግ ፍጹም አፓርታዳዊ (ዘረኛ እና አግላይ) አካሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ከዚህም ባሻገር፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ እንደ መሆኗ መጠን፤ የየትኛውም ሕዝብ መብት ሳይደፈጥጥ የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ይዞታ ሆና መቀጠል አለባት።
በመሆኑም፣ ምንም እንኳን አንዱ አካል በመንግሥት ስር ሆኖ በሕጋዊና በአገራዊ ምክክር መድረኮች ተቀምጦ ቢሆንም፣ ሌላው አካል ደግሞ ሀገር አፈርሳለኹ ብሎ በትጥቅ ትግል ላይ ያለ ቢሆንም፣ የሁለቱም ዓላማ አዲስ አበባን ከኢትዮጰያዊያን ማዕከልነቷ ነጥሎ ወደ ኦሮሚያ ክልል ማጠቃለል ነው። ይህ አካሄድ የከተማዋን ነዋሪዎች ሰላም፣ የከተማዋን ነፃ የአስተዳደር መዋቅር እና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን በመሆኑ በጥብቅ እንቃወመዋለን፤ እናወግዘዋለንም።
ስንተባበር እንጠነክራለን፣ እናሸንፋለን!!
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት
—
ነሃሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም
