ከአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ—ሰኔ 17፣ 2018 ዓ.ም።
/
የእነ አርበኛ አማረ አቸነፍ የክብር መስዋዕትነት ትግል አሻጋሪ ነው !!!
/
የአማራ ሕዝብ በአገዛዙ የተከፈተበትን ነገዳዊ ማንነት ተኮር ጦርነት መክቶ ለማክሸፍ ነፍጡን መዝዞ ዱርን ቤቴ ብሎ መታገል ከጀመረ ሶስተኛ ዓመቱን ጨርሶ ወደ አራተኛ ዓመት እየተሸጋገረ ይገኛል።
በዚህ እልህ አስጨራሽ ግን የተቀደሰ የህልውና ትግል፣ ብርቅዬ ጀግኖች ምትክ የለሽ ውድ ህይወታቸውን በክብር ሰውተዋል። ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ ም ፣ የኦህዴድ አገዛዝ በሜካናይዝድ የታጀበ በርካታ ሰራዊት ይዞ፣
በማዕካለዊ ጎንደር ደንቢያ እና ማክሰኝት ዙሪያ በአፋብን ጎንደር ጠቅላይ ግዛት በላይ እዝ ላይ የማጥቃት ዘመቻ ከፍቷል።
የአገዛዙ መደበኛ ኃይል በልዩ ሁኔታ ከፍተኛ ዝግጅት ባደረገበት በዚህ ዘመቻ፣ ወደ ቀጠናው የገባው በምስለኔው ብአዴን እና ሰርጎ ገቦች መንገድ መሪነት የነበረ ሲሆን፣ ወደ ፋኖ ጦር ተስቦ የፋኖ መሪዎችን ከበባ ውስጥ የማስገባት እቅድ ነበረው።ይህንን የከበባ እንቅስቃሴ ያስተዋለው ክንደ ነበልባሉ የአማራ ፋኖ፣ ከበባውን ለመስበር ብርቱ ፍልሚያ በማድረግ አይቀጡ አድርሶበታል።
በዚህ ብርቱ ውጊያ የአማራ ፋኖ በርካታ የአገዛዙን ሠራዊት ሙት እና ቁስለኛ በማድረግ እቅዱን በአመዛኙ ማክሸፍ የተቻለ ቢሆንም፣ በፋኖ በኩል እንቁ ጀግኖች የክብር ሰማእትነትን ተቀብለዋል። በዚህም የአማራ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች እና የፋኖ አመራሮች የሆኑት አርበኛ አማረ አቸነፍ ታደገ፣ አርበኛ ሳምሶን አማረ፣ አርበኛ መቶ አለቃ አበራ አግማስ፣ አርበኛ ሥጦት ጀምበር፣ አርበኛ አትርሳው ገበያውን ጨምሮ ሌሎች ጀግኖች የሞትን ፅዋ በጀግንነት ተቀብለዋል።
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በብርቅዬ ጀግኖቹ የክብር መስዋእትነት እጅግ ጥልቅ ሀዘን ቢሰማውም፣ በጀግኖቹ አንጸባራቂ ተጋድሎ እና የክብር መስዋእትነት አድናቆት እና ኩራት የተሰማውም መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ነፃነት ያለ ትግል፣ ትግል ደግሞ ያለመስዋእትነት ከቶም ቢሆን የሚታሰብ አይደለምና፣ ጀግኖቹ እጅ ሰጥተው ህይወታቸውን ከማስቀጠል ይልቅ “እናንተ ውጡ፣ እኛ መውጣት አንችልም። እኛ የምንወጣው በጠላት ሬሳ ላይ ተረማምደን ነው።አንድነታችንን የሚናፍቀውን ህዝባችንን እንድታበስሩት አደራ እንላለን” በማለት ለትግል አጋሮቻቸው ሽፋን በመስጠት ህይወታቸውን ለቆሙለት የተቀደሰ ዓላማ በክብር በመስጠታቸው፣ ዘመን ተሻጋሪ አሽራ ያኖሩ የቁርጥ ቀን የህዝብ ልጆች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የህይወት መስዋዕትነታቸውም ለአማራ ህዝብ የመኖር መብት መከበር ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጰያዊያን ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነትም የተከፈለ ነው። ክብር እና ታሪካቸውም ሀገራዊ ነው።
ታጋይ ይሰዋል፣ ትግሉ ግን በታጋዮች ይቀጥላል። የጀግኖቹ አስደናቂ ተጋድሎ እና አንጸባራቂ መስዋእትነት፣ መላውን የአማራ ፋኖ የቆመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይበልጥ እንደሚያነሳሳው እና እንደሚያፀናው በጽኑ እናምናለን።
ፈጣሪ የጀግኖቹን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን፣ ዘመዶቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ያፅናናልን።
ስንተባበር እንጠነክራለን፣ እናሸንፋለን!!
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት
ሰኔ 17 ቀን 2018
