አዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት
Addis Ababa Mefia Council.
—
2019 ለመላ ኢትዮጵያዊያን የድል፣የፍትሕ እና የሰላም ዓመት ይሁንልን!!!
.—
—በህልውና አደጋ ላይ ያለኸው የተከበርከው የአዲስ አበባ ህዝብ፣
በተገባደደው 2018 ዓ ም አዲስ አበባን ለመሰልቀጥ የተነሳው ኦህዴድ መራሹ የብልጽግና አገዛዝ፣ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ይህ ቀረሽ የማይበል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባሕላዊና ስነ ልቦናዊ በደል የፈፀመበት ዓመት ነበር።
የአዲስ አበባ ህዝብ ጥረህ ግረህ ያፈራህው ሀብት እና ንብረት በኮሪዶል “ልማት” ስም ያለበቂ ካሳ እና ምትክ ንብረትህን አፍርሶብሃል፣ በንግድ ስራ ላይ በተሰማራኸው ላይ ደግሞ ከመርካቶ እስከ የካ ተራራ፣ ከቦሌ እስከ ላፍቶ፣ ከንፋስ ስልክ እስከ ተክለኃይማኖት፣ ከጎተራ እስከ አራት እና ስድስት ኪሎ፣ከፒያሳ አራዳ እስከ ለገሃር ሜኪሲኮ የማፍረስ ተግባር ፈጽሞብሃል፣ መነሻ ካፒታላቸው 10.000ሺ ብር በሆኑ ሱቅ በደረቴ ነጋዴዎች ላይ ከ100.000ሺህ ብር ብር በላይ ግብር እና ታክስ ከመጣል ጀምሮ የንግዱን ማህበረሰብ ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ እና የነጋዴውን ገቢ እና ወጪን ያላገናዘበ ከፍተኛ ግብር በመጣል ከፍተኛ በደል ተፈፅሞብሃል። እስከመቼ ነው ዝም ብለህ የምትኖረው?
የሰርቶ አደሩን ክፍል የተመለከትን እንደሆነ፣ በኑሮ ውድነት አለንጋ ክፉኛ እየተገረፈ መኖር የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በአጠቃላይ 2018 ዓ ም ለአዲስ አበባ እና ለአዲስ አበቤ እጅግ ፈታኝ ዓመት ነበር። ይህ አልበቃ ብሎ፣ በዓመቱ መገባደጃ በወርሃ ሐምሌ እና ነሃሴ በተካሄደው የአገዛዙ “ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ” ተብዬ ኦህዴድ/ብልጽግና “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት” የሚል አንቀፅ በህገመንግሥቱ እንዲካተት ውሳኔ አስተላልፎ፣ በከተማዋ ላይ ላንዣበበው የጄኖሳይድ አደጋ የህግ ማዕቀፍ ተበጅቶለታል።
“አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት” የሚለውን ኦህዴዳዊ ውሳኔ በምክክር ጉባኤ ተብዬ ላይ የተወሰነ እርቀት ቢሄዱበትም፣ ይህን ምኞታቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ገና ብዙ መንገድ የሚቀር በመሆኑ፣ ምኞታቸው ቅዥታቸው ሆኖ ያልፍ ዘንድ 2019 ዓመት አዲስ አበባን ከኦህዴድ መንጋጋ ፈልቅቀን ነጻ የምናወጣበት የትግል እና የድል ዓመት ይሆንልን ዘንድ የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት ጥብቅ የትግል ጥሪውን እያስተላለፈ፣ አዲሱ ዓመት የድል፣ የፍትህ፣የእኩልነት፣ የሰላም ይሆንልን ዘንድ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
— በህልውና ትግል ላይ ያለኸው የተከበርከው የአማራ ህዝብ፣
ባገባደድነው 2018 ዓመት የአማራ ሕዝብ በ2015 የተጀመረው የህልውና ትግል ሶስተኛ ዓመቱን ያጠናቀቀበት የትግል፣ የድልና የመስዋእትነት ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። አገዛዙ በአራቱም የአማራ ጠቅላይ ግዛቶች እየተመላለሰ ንጹሃንን በድሮን፣ በጄት፣ በዙ -23፣ በዲሽቃ እና በእግረኛ ሰራዊት በግፍ ጨፍጭፋል፣ የአማራ ፋኖም የአጸፋ ምላሽ በመስጠት ብርቱ ዋጋ ያስከፈለ ኪሳራ አድርሶበታል።
በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ምትክ የለሽ ብርቅዬ ህይወታቸውን ለነገደ አማራ ሕዝብ ህልውና እና ለመላ ኢትዮጰያዊያን ሁለንተናዊ ነጻነት ብለው የተሰውቱን ድንቅ የፋኖ አባላት የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት ከልቡ ይዘክራል፣ በእጅጉም ያከብራል።
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት መጪው 2019 አዲስ ዓመት በድል የታጀበ የትግል፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ይሆን ዘንድ መልካሙን ምኞቱን ይገልጻል። የአማራ እና የአዲስ አበባ የህልውና የትግል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነው።
— ሀገራዊ የህልውና አደጋ የተጋረጠብህ የተከበርከው የኢትዮጰያ ህዝብ፣
2018 ሀገራችን ኢትዮጲያ በእርሰ በእርስ ውስጣዊ ጦርነት፣ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ በአገዝዙ መደበኛ እና ኢ- መደበኛ ታጣቂዎች ንጹሀን ዜጎች በማንነታቸው እየተመረጡ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በሸዋ ፣ በጅማ፣ በመተከል እና በሌሎች አካባቢዎች በግፍ ተጭፍጭፈው የተገደሉበት፣ ሀብትና ንብረታቸውን እየተነጠቁ የተዘረፉበት እና ከትውልድ ቄያቸው እየተፈናቀሉ የተባረሩበት ዓመት ነበር።
አገዛዙ በአማራ ክልል የለኮሰው የእርሰ በእርስ ጦርነት ተጠናክሮ ሶስተኛውን ዓመት አገባዶ ወደ አራተኛ ዓመት የተሸጋገረ ሲሆን፣ ትግራይ ክማእከላዊው መንግስት አፈንግጣ በዲ ፋክቶ ስቴት ደረጃ ያለችበት ሁኔታ ነው ያለው።
የኢትዮጲያ ገንዘብ የመግዛት አቅም እጅግ አሽቆልቁሎ የመንግስትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ሰራተኞች በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ “የሰራተኛ ተመጽዋች” ሆነው ለከፋ ችግር ተዳርገዋል። የኑሮ ውድነቱ ከእርስ በእርስ ጦርነቱ ባልተናነሰ ሁኔታ በህዝብ ላይ የተጫነ ሸክም ሆኗል።
መጪው አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበት መከራ የሚቀጥልበት እንዳይሆን፣ አገዛዙን በጽናት፣ በትጋት፣ በተባበረ አንድነት ቆርጠን የምንታገልበት የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሁለንተናዊ ነጻነት እና ሰላም ዘመንን የምንቀበልበት እንዲሆን ልባዊ ምኞታችንን እንገልፃለን። በዚህ ረገድ፣ የበኩላችንን ጠጠር እንወረውራለን።
ስንተባበር፣ እንጠነክራለን- እናሸንፋለን !!!
—
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት፣
ጳጉሜ 5፣ 2018 ዓ ም
