አዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት

Addis Ababa Media Council.

/

የአዳነች አቤቤ ታላቁ ክህደት!!!

/

ሐምሌ 23፣ 2018 ዓ.ም

/

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ተብለው በስልጣን ላይ ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባኤ ከአቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመቀናጀት አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንድትካለል ይፋዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ወይዘሮዋ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ላይ ተቆርሶ የተፈጠረውን ሸገር ሲቲን ለእነ ሽመልስ አብዲሳ አሳልፈው በመስጠት እና አዲስ አበባ አስተዳደራዊ ነፃነቷን እንድትገፈፍ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ካድሬዎች እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ አዲስ አበባን ወክለው ለአስተዳደራዊ ነፃነቷ እና መብቶቿ መከራከር ሲገባቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ስር መካለል አለባት በማለት ታላቁን ክህደት እየፈፀሙ ይገኛሉ። 

አዲስ አበባን በኦሮሚያ ስር ለማካተት የሚያስችል አንዳችም ዓይነት የታሪክ፣ የሥነልቦና፣ የቋንቋ፣ የህዝብ ስብጥር እና ፍላጎት የለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ፣ እነ አዳነች አበቤ ከተማዋን በግድ ወደ ኦሮሚያ ለመጠቅለል ወስነው በኢትዮጰያ አቻ የሌለውን የአፓርታይድ ሥርዓት ዘርግተዋል። ለዚህም እንደ ዋነኛ ማሳያ የሆነው፣ በአፓርታይድ ዘመን በደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ህፃናት የነጮቹን አፍሪካነርስ ቋንቋ በትምህርት ቤቶች በግዳጅ ይማሩ እንደነበረው፣ የአዲስ አበባ ህፃናት የእነ ዐቢይ አህመድ እና አዳነች አበቤ አፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን ኦሮምኛ በትምህርት ቤቶች በግዳጅ እንዲማሩ እየተደረገ ይገኛሉ።

 ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነታቸው ታማኝነታቸው ለአዲስ አበባ ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ ለተወለዱበት ኦሮሚያ እና ኦህዴድ/ብልፅግና ማድረጋቸው ከተማዋን ለመምራት የሚያስችል ፖለቲካዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ሞራላዊ ቁመና እንደሌላቸው ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን አምነው፣ ከተቻለ ከከንቲባነታቸው በፍቃዳቸው ቢለቁ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ይሰራሉ። በፍቃዳቸው ካልለቀቁ በህዝባዊ ትግል መልቀቅ አለባቸው። አዲስ አበባ ለአስተዳደራዊ ነፃነቷ የሚከራከርላት መሪ ያስፈልጋታል። 

ስለሆነም፣ አዲስ አበባ ለከተማዋ ህልውና እና ሁለንተናዊ ጥቅም በሚሰሩ ልጆች መመራት እና መወከል ስላለባት፣ አዳነች አቤቤ ከከንቲባነት እንዲነሱ የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በጥብቅ ይጠይቃል፣ የወይዘሮዋንም የክህደት አቋም እጅግ አጥብቆ ያወግዛል። ህዝቡም በቀጣይነት ለሚቀርቡ የትግል ጥሪዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ በአንክሮ እንጠይቃለን።

/

ስንተባበር እንጠነክራለን፣ እናሸንፋለን !!!

/

የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት

ሐምሌ 23፣ 2018 ዓ.ም።